227 ሺሕ 519 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ

ሚያዝያ 17/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ ባለፉት 9 ወራት 227 ሺሕ 519 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ባደረገው የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ነው ይህንን ያስታወቀው፡፡

የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከሆኑት አዲስ ደንበኞች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የድህረ ክፍያ ደንበኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የቅድመ ክፍያ ደንበኞች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም አዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራው ስራ 80 የገጠር ከተሞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡

አዳዲስ ከተሞችንና መንደሮቹን ተጠቃሚ ለማድረግ 844 ነጥብ 23 ኪ.ሜ የመካከለኛ እና 1 ሺሕ 216 ነጥብ 94 ኪ.ሜ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም 242 ትራንስፎርመሮችን የመትከል ስራዎች ተከናውነዋልም ነው የተባለው፡፡

ተቋሙ የደንበኛን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን የሀገሪቱ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሽፋንም 48 በመቶ መድረሱ ተመላክቷል፡፡

ተቋሙ በቀጣይ ጊዜያት አዲስ ኃይል ፈላጊ ደንበኞችን ቁጥር ማሳደግ፣ የተቋሙን ገቢ በወቅቱና ውጤታማ በሆነ መንገድ መሰብሰብ፣ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅን መቀነስ እና ደንበኛ ተኮርና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አመላክቷል፡፡