የግብርና አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ ግብርና እየተሸጋገረች መሆኗ የታየበት ነው

ግንቦት 8/2015 (ዋልታ) በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለው የግብርና አውደ ርዕይ ኢትዮጵያ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ግብርና ወደ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርና እየተሸጋገረች መሆኗ የታየበት ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቲ ተናገሩ፡፡

ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ በሚል መሪ ቃል የግብርና አውደ ርዕይ ሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም መከፈቱ የሚታወስ ነው፡፡

አውደ ርዕዩን በአገሪቱ ውስጥ ካሉ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች እየጎበኙ ይገኛሉ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቲ አገራችን ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ግብርና ወደ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርና እየተሸጋገረች መሆኗን ያየንበት ነው ብለዋል።

ግብርና በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ብቻ ሳይሆን በከተማም ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሳይቷል ብለዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ ከተማ አስተዳደሩ የከተማ ግብርናን እንደ አማራጭ በመውሰድ ከገቢ ምንጭነት ባሻገር ለዜጎች የስራ እድልን መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

በዚህም ከ300 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና ተሳታፊ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄ ያለውን የግብርና ኤግዝቢሽን የጎበኙት የሚዲያ ባለሙያዎች በበኩላቸው ከባህላዊ የግብርና ስርዓት ጀምሮ አለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የተጠቀመችው ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ ለመቻል ብሎም ምርቶችን ለአለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳላት ለመገንዘብ ችለናል ብለዋል።

በቁምነገር አህመድ