በመጀመሪያ ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸው ተገለጸ

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

ግንቦት 11/2015 (ዋልታ) በመጀመሪያ ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 25 ቢሊዮን የተለያዩ የደንና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በቅርቡ የሚጀመረውን የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በውጤታማነት ለመፈፀም “አረንጓዴ አሻራችን ለዘላቂ ልማታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም በተከናወነው በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 25 ቢሊዮን የተለያዩ የደንና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው ከ225 ሺሕ በላይ የችግኞችን በጎረቤት ሀገራት በመትከል ድንበር ተሻጋሪ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ በጋራ ለመከላከል መልካም ጅምሮች እንደሆነ ገልጸዋል።

ከ2003 ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ማህበረሰቡን ያሳተፈ የተፋሰስ ልማት የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስና ለምነቱ እንዲጨምር፣ የእፅዋት ደን ሽፋን እንዲጨምር፣ የገፀ እና የከርሰ ምድር ውሃ መጠን፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረጉም ባሻገር የአርሶ አደሩ ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚያም ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለም ጠቁመዋል።

በፓናል ውይይቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ አረንጓዴ አሻራን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ አምስቱን “መዎች” መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

እነዚህም መረዳት፣ መዘጋጀት፣ መትከል፣ መንከባከብ እና መጠቀም መሆናቸውን ጠቅሰው የአረንጓዴ አሻራን ዓላማ መረዳት፣ መርኃ ግብሩን ለማሳካት ፈጻሚ አካላትን ማዘጋጀት፣ በመርኃ ግብሩ የተለያዩ ችግኞችን መትከል፣ የተተከሉ ችግኞችን ጽድቀት መከታተልና መንከባከብ እንዲሁም በለሙ ዛፎች ሕዝቡን ብሎም አገሪቱን በዘላቂነት የደን ተጠቃሚ ማድረግና ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ልማት መመስረት መቻል ይኖብናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለዓለም አቀፍ እና አኅጉር አቀፍ አጀንዳዎች በቀጥታ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ እድናቆትንና ዕውቅና ማግኘቷንም ገልጸዋል።

የፌዴራል እና ክልል ባለድርሻ አካላት በአንደኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የታየውን ቁርጠኝነትና ትጋት በ2ኛው ምዕራፍ በላቀ ደረጃ እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።

በሳራ ስዩም