መንግስት ለጨረታ ያቀረባቸውን ስምንት የስኳር ፋብሪካዎች ለመግዛት ፍላጎት ላሳዩ ባለሃብቶች ዝርዝር የጨረታ ሰነድ ይፋ አደረገ

ግንቦት 15/2015 (ዋልታ) መንግስት ለጨረታ ያቀረባቸውን ስምንት የስኳር ፋብሪካዎች ለመግዛት ፍላጎት ላሳዩ ባለሀብቶች ዝርዝር የጨረታ ሰነድ ማዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግሥት በነሐሴ 2014 የገንዘብ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል በአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዘዋወር ባወጣው ጨረታ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።

የፍላጎት መግለጫውን ተከትሎ ከ20 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ፍላጎት ማሳየታቸው አይዘነጋም።

ኦሞ ኩራዝ 1፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3፣ ኦሞ ኩራዝ 5፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ ለጨረታ የቀረቡት የስኳር ፋብሪካዎች ሲሆኑ የገንዘብ ሚኒስቴር የጨረታ አጠቃላይ ሂደቱን በዝርዝር የሚያሳይ ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልጿል።

ሰነዱ የፋብሪካዎቹን ሽያጭ፣ ተጫራቾች ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች፣ የግምገማ ቅድመ ሁኔታዎች፣ ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ስፋት (ስኮፕ) እና የጨረታ ጊዜ ገደብ አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎችን መያዙን አስታውቋል።

ዝርዝር የጨረታ ሰነዱ የመንግስትን የስኳር ዘርፉን ወደ ተወዳዳሪ ገበያ ማስገባትና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የማጠናከር ሽግግር ጥረቶች ወሳኝ ምዕራፍ የሚባሉ መሆናቸውን ገልጿል።

የስኳር ፋብሪካዎቹን ለመግዛት ፍላጎት ያሳዩ ፋብሪካዎች አሁንም በጨረታው ሂደት መሳተፋቸውን እንዲቀጥሉ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል።

የፋብሪካዎቹ ወደ ግል ይዞታ የመዞር ሂደት ስኬታማነት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገትና ልማት እንዲሁም በአገሪቷ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጿል።