ልሂቃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክር ሂደት በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ

መብራቱ አለሙ (ዶ/ር)

ሰኔ 5/2015 (ዋልታ) በአገራዊ ምክክሩ ሂደት ልሂቃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) የአገራዊ ምክክሩ አላማ በማያግባቡ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመካክሮ ችግሮችን መፍታትና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።

አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ደግሞ ልሂቃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማኅበረሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ መንግሥት፣ የተለያዩ ማህበራትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ አስረድተዋል።

አገሪቱ በተለያዩ ግጭቶች እንደማለፏ የምክክሩ ፋይዳ የጎላ ነው ያሉት ሰብሳቢው ዕውነተኛ ምክክር ለማድረግ ሁሉን አሳታፊና እና ተጨባጭ ውጤት ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው አገራዊ ምክክር ትርክቶችን በማስቆም ዘላቂ ሰላም በማስፈን እንዲሁም በመንግሥትና ኅብረተሰቡ መካከል ያለውን መስተጋብር በማዳበር ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በሚደረጉት የምክክር መድረኮች ሃሳብን በነፃነት በማንሳትና በሰከነ መንፈስ በመምከር ለአገር የሚበጅ ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምሁራን በበኩላቸው በምክክሩ ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀት፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ የቀጣይ አቅጣጫዎችን መለየትና አንኳር ሃሳቦችን ማንሳት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይ በሚደረገው አገራዊ ምክክር ላይ አንድን ብሔር ጠል ሃሳቦችና ትርክቶችን እንዲቀረፉ ማድረግና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል ያሉት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ በምክክሩ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ የተጠናከረ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ያላቸውን በርካታ ጥያቄዎች በአግባቡ ለማስተናገድና በአገሪቱ ያሉ የሀሰት ትርክቶችን መቋጫ ለማበጀት ብሔራዊ ምክክሩ እንደጥሩ አጋጣሚ የሚወሰድ መሆኑን አንስተዋል።

ምክክሩ ሰላምን ከማስፈን ባለፈ ወደፊት አገሪቱ ልትመራበት የምትችልበትን አጀንዳ ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ መላው ሕዝብ ለምክክሩ መሳካት የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደት ላይ የሃይማኖት ተቋማት፣ ዲያስፖራዎች፣ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዜጎች እንደ አገር ምክክር ሊደረግባቸው ይገባል ብለው የሚያምኑባቸውን ጉዳዮች እንዲጠቁሙና ለዚህ አገራዊ ጉዳይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአካል በመገኘት ወይም በስልክ ቁጥር 0111261196፤ 0975554500፣ በፖስታ ሳጥን ቁጥር 32623 እንዲሁም በኢሜይል አድራሻ ethiopianndc@gmail.com ጉዳያቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ማስታወቁ ይታወሳል።