ባንኮች የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ አለባቸው – የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

ነሐሴ 27/2015 (አዲስ ዋልታ) ባንኮች የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል አገልግሎት የሚሰጥበትና ደንበኞች ራሳቸውን የሚያስተናግዱበት ዓቢይ ቅርንጫፍ ዛሬ አስጀምሯል።

በአዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘውን ዓቢይ ቅርንጫፍ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ መርቀው የከፈቱ ሲሆን ባንኮች እየዘመነ የመጣውን የዘርፉን እድገት በሚመጥን መልኩ ራሳቸውን ማብቃት አለባቸው ብለዋል።

ለዚህም ባንኮች የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘና ይበልጥ ቀልጣፋ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ያስጀመረው ዲጂታል ዓቢይ ቅርንጫፍ የባንኩን ዘመናዊ አሰራር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሌሎች ባንኮችም ተመሳሳይ የዲጂታል የማስፋፊያ ሥራ በስፋት በመሥራት የአገልግሎት ደረጃቸውን ሊያሻሽሉ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው በዓቢይ ቅርንጫፉ ሁሉም አገልግሎቶች በዲጂታል እንደሚሰጥ ተናግረው ደንበኞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ተጠቅመው የሚስተናገዱበት መሆኑን ጠቀመዋል።

የባንኩ ዓቢይ ቅርንጫፍ መከፈት ለታላላቅና ኮርፖሬት ደንበኞች የሚሰጠውን የአገልግሎት ጥራት ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

በቅርንጫፉ አዲስ ሒሳብ ለሚከፈቱ ደንበኞች በዲጂታል ሥርዓት ፎቶና ፊርማ የሚቀበል መሆኑንም ተናግረዋል።

ባንኩ በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፉን በማዘመን የዲጂታል ኢኮኖሚን ዕውን ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።