ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡ በዓላትን ሲያከብር የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳሰበ

መስከረም 15/2016 (አዲስ ዋልታ) ኅብረተሰቡ የመውሊድ፣ ደመራ እና መስቀል በዓላትን ሲያከብር የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት በተለይ የደመራ በዓል እሳት ከመለኮስ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የእሳት አደጋ ሊያጋጥም የሚችልበት ዕድል ሰፊ ስለሆነ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

በዚህም ደመራው በሚደመርበት ወቅት ቦታውን ከመምረጥ ጀምሮ የኤሌክትሪክና ቴሌኮሙዩኒኬሽን መስመሮች አለመኖራቸውን፣ የነዳጅ ማዳያ፣ የጋራጅ ቤቶች እንዲሁም የመሳሰሉ የእሳት አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ተጋላጭ ሁኔታዎች በመራቅ መሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የችቦ ቁጥር ሲበዛ እሳቱም በዛው ልክ ስለሚሰፋ ለሥነ ሥርዓቱ ብቻ የሚያስፈልግ የችቦ መጠን መጠቀም እንደሚገባም መክረዋል፡፡

በመጨረሻም የደመራ መለኮስ ሥነ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ እሳቱን በውሃ አጥፍቶ ወደ ቤት መግባት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

ለዚህም በተለያዩ መንገዶች ከኮሚሽኑ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን መተግበር እንደሚገባም ባለሙያው አሳስበዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለሚፈጠሩ ማንኛውም አደጋ ምላሽ ለመስጠት በ10 ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችና በማዕከል ዝግጅት ማጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ አደጋዎች ሲያጋጥሙ በነፃ የስልክ መስመር 939 እንዲሁም በቀጥታ የስልክ መስመሮች 0111555300 ወይም በ0111568601 በመደወል ለኮሚሽኑ ማሳወቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በአድማሱ አራጋው