በዲጂታል የክፍያ አማራጮች አማካኝነት በዓመት እስከ አራት ትሪሊዮን ብር እየተዘዋወረ መሆኑ ተጠቆመ

እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

መስከረም 21/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ በዲጂታል የክፍያ አማራጮች አማካኝነት በዓመት እስከ አራት ትሪሊዮን ብር እየተዘዋወረ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ አማራጭ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር እንዲቀንስ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸው በዓመት እስከ አራት ትሪሊዮን የሚደርስ ብር በዲጂታል የክፍያ አማራጮች እንደሚዘዋወር አመላክተዋል።

ሁለተኛውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ባለፉት ሁለት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን አንስተዋል።

ዲጂታል የክፍያ አማራጮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተተገበሩ በመሆኑ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ሊቀንስ እንደቻለና መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጥ የሚደረግባቸው ግብይቶች በዲጂታል እንዲከናወኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከ170 በላይ የመንግሥት ተቋማት የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ውስጥ መግባታቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ግብ ለማሳካት በመንግሥት አገልግሎቶች፣ በንግድ ሥራዎች የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችን በዲጅታል የክፍያ አማራጮች መጠቀምና የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ማስቀረት ይገባል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች የዕለት ተዕለት ግብይታቸውን ጥሬ ገንዘብ ይዘው መሄድ ሳያስፈልጋቸው በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የሚፈልጉትን ሥራ እያከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።

በሀገሪቱ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ዘመን ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎች በማስተዋወቅና የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ የራቀ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር እየተሠራ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይም የክፍያ ሥርዓትን ማዘመንና ተደራሽነቱን የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተው ዲጂታል የክፍያ አማራጮች ወጪን በመቆጠብ፣ የፋይናንስ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለማስቀረት፣ የዲጂታል ግብይት ተደራሽነትን ለማስፋፋትና ግልጽነት ያለው ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እገዛ እንደሚያደርግም አብራርተዋል፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ከተቻለ የንግዱን ዘርፍ አገልግሎት ማሻሻል እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ዘመናዊ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዲጂታል የፋይናስ ሥርዓትን የማጠናከር ዓላማ እንዳለው አስታውቀዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አራት ቁልፍ ምሰሶዎች እንዳሉት ጠቁመው የማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት፣ የግሉ ዘርፍ ንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻል፣ የአየር ንብረትን በማሻሻል ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ብቃት ያለው የሲቪል ሰርቪስ መፍጠር ላይ ትኩረት መደረጉን መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡