ማዕከላዊ እዝ ስኬታማ ግዳጁን በብቃት እያስቀጠለ ነው – ጄኔራል አበባው ታደሰ

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ

መስከረም 26/2016 (አዲስ ዋልታ) ማዕከላዊ እዝ እየፈፀመ የመጣውን ስኬታማ ግዳጅ በላቀ ብቃት እያስቀጠለ ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ ገለጹ፡፡

ጀኔራል አበባው ከማዕከላዊ እዝ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በግዳጅ አፈፃፀም ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በቀጠናው የሚንቀሳቀሰው ሸኔ የተባለው የጥፋት ቡድን ህዝብን ሲዘርፍ እና ሲያሰቃይ የነበረ ቢሆንም ዕዙ ይህንኑ ቡድን ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ በሚያስችል አግባብ ተልዕኮውን እየፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።

ማእከላዊ እዝ እንደ እዝ መልካም ተግባራቶቹን አቅቦ በመጓዝ ይበልጥ በውጤት የሚለካ ስራ በዘላቂነት መስራት ይኖርበታል ያሉት ጀኔራል አበባው ታደሰ ይህን ለማስቀጠልም የማያቋርጥ የስነ-ልቦና ስራዎችን በየደረጃው ያለ የእዙ አመራር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

የእዙ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ በበኩላቸው በአነስተኛ ኃይል የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ክፍሎችን የመፍጠሩ ሂደት በትኩረት እየተሠራበት ነው ብለዋል፡፡

የእዙ የሰራዊት አባላት በራስ መተማመን ያለውና የሚሰጠውን ማንኛውንም ግዳጅ በላቀ ውጤት እየፈፀመ ይገኛል ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡