“ጀፎር” የጉራጌዎች ሀገር በቀል የምህንድስና ጥበብ

 


#ሀገሬ

በሠራዊት ሸሎ

ጉራጌ ብዙ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ሲሆን የመንደር አመሰራረቱና ጀፎር የተሰኘው የባህላዊ የአውራ መንገድ ቅየሣ ወይም የምሕንድስና ጥበብ አንዱ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

“ጀፎር” ማለት የጉራጌኛ ቃል ሲሆን አውራ መንገድ ማለት ነው፡፡

ታዲያ ይህ የ”ጀፎር” ፍልስፍና በጉራጌዎች መንደር የተጀመረው ገና በአገራችን ባለ አራት እግር የሞተር ተሽከርካሪዎች ሳይገቡና የመኪና ስሙ እንኳን በማይታወቅበት በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደነበረ የጉሬጌ አባቶች ይናገራሉ።

የጉራጌዎቹ የመንደር አመሰራረት እና ጀፎረ ወይም የባህላዊ አውራ መንገዱ የማይነጣጠሉና በአሁኑ የሳይንሳዊ የምህንድስና ስሌት መሠረት ባለሁለት ተካፋዮች ያሉትን የአውራ ጎዳና መንገድ የሚመስል የአባቶች የጥበብ አሻራ ያረፈበት ነው፡፡ ይህ ጥበብ የጉራጌ አባቶች ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ሲተግብሩት የኖረና ለአሁኑ ትውልድ የደረሰ እሴትና የሚያስደንቅ ትውፊት ነው፡፡

የጀፎር የጎኑ ስፋት ከ60-100 ሜትር እንደሚወስድ የሚገለጽ ሲሆን ርዝመቱ ግን አውራ መንገድ (ጀፎር) በሚያቋርጥባቸው አቅጣጫዎች ወንዝ፣ ደንና ትልልቅ ሸለቆዎች እስካላጋጠው ድረስ ቅያሱ ይቀጥላል፡፡ የመንገዱ ስፋት የሚለካውም በባህሉ መሠረት በተመረጡ አባቶች ወይም የመሬት ልኬት ዳኞች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጀፎር በሁለት መንደሮች ትዩይ በመካከላቸው አቋርጦ የሚያልፍና አረንጓዴ ሳር የለበሰ ውብና ጽዱ ባህላዊ አውራ መንገድ ነው።

ይህ በጉራጌ አባቶች ሀገር በቀል ዕውቀት የተጀመረው ባህላዊ የመንደር አመሠራረትና የአውራ መንገድ ቅየሣ ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ትኩረት የሰጠና መሠረት ያደረገ መሆኑ ደግሞ የአባቶችን የአርቆ አሳቢነትና ጥልቅ የጥበብ ባለቤትነትን የሚያስረዳ ስለመሆኑ አይካድም።

ጀፎር መሃሉን አቋርጦ በሚያልፈበት ዳርና ዳር የሚታዩ መንደሮች በጉራጌዎች ጥበብ ተክነውና በሀገር በቀል ቁሳቁሶች የተሠሩ የጉራጌ ባህላዊ የጎጆ ቤቶች አይን የሚማርክ ገፅታ አላቸው።

ውብ የሆነው የባህላዊ አውራ መንገድ (ጀፎር) የአከባቢ ነዋሪዎች መግቢያና መውጫ ሆኖ ከማገልገል ባሻገር የተላያዩ ማህባራዊና ሀይማኖታዊ ኩነቶችን ለማካሄድ በጋራ የሚጠቀሙበት የወል ሥፍራም ነው፡፡

ሰፊ ስብሰባዎች ሲኖሩ የሚደረግበት፣ ባህላዊ የእርቅ ሥነ ስርዓት የሚከናወንበት፣ በመስቀል በዓል የደመራ ስነስርዓት የሚካድበት ነው፡፡ በሠርግ ጊዜም ሰርገኞች የሚጨፍሩበት፣ አባቶችና እናቶች ዘመድ አዝማድ ተሰባስበው ልጆቻቸውን መርቀው ለሀማች የሚሰጡበት ቦታ መሆኑም ይነገርለታል፡፡ ሰው ቢሞት በሀዘን ጊዜም የለቅሶ ስነስርዓት የሚከናወነው በዚሁ ሥፍራ ነው፡፡

በተጨማሪም ሥፍራው የፈረስ ጉግስና የተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች የሚካሄዱበት ሲሆን ለከብቶች መውጫና መግቢያ እንዲሁም ለመዋያነትም እንደሚያገለግል ይገለጻል።

ጀፎር ህፃናት ይቦረቁበታል፣ ወጣቶች የገና ጨዋታ ይጫወቱበታል፡፡ በመስቀል በዓል ዕለት ወጣት ሴቶችና ወንዶች ከደመራው ሥነ ሥርዓት በኋላ ባህላዊ ጨዋታዎችን ይጫውቱበታል፡፡ ብቻ የጀፎር ጠቀሜታዎች ከብዙ ጥቂቱን ጠቅስን እንጂ አከባቢውን ቢጎበኙት ብዙ አስተማሪ ቁምነገሮችን ከጉራጌ አባቶች አሻራ ይገበያሉ፡፡

ባህላዊ አውራ መንገዱ (ጀፎር) ለብዙ ዘመናት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ለዘመናት የተሻገረው አባቶች በባህላዊ መንገድ የሚዳኝበትን ህግ አርቅቀው በሥራ ላይ በማዋላቸው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ጀፎር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ዛሬ ድረስ የሚጠበቅበትን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣውን ባህላዊ አውራ መንገድን (ጀፎርን) እያንዳንዱ የመንደሩ ነዋሪ የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ሁሉም የመንደሩ ነዋሪ በነቂስ በመውጣትም በባለቤትነት ስሜት ጀፎርን የሚያጸዳበት ሥርዓትም ተበጅቶለታል።

የጉራጌ ማህበረሰብ ለጀፎር ትልቅ ትኩረት ከመስጠቱ የተነሳ ጀፎር ላይ ከተተከለ የዛፍ ቅርንጫፍ ጀምሮ ሌሎች በባህላዊ አውራ መንገድ ይዞታ ውስጥ ያሉ የወል ንብረቶችን ለግል ጥቅም ማዋል ክልክል ነው።

በጉራጌዎች ዘንድ የባህላዊ አውራ መንገድን ወይም ጀፎርን አጥሮ ለግል ይዞታ ማዋልም የተከለከለና የተወገዘ ተግባር መሆኑን አባቶች ይስማሙበታል፡፡ ማንኛውም ግለሰብ የጀፎረን ይዞታ ቢነካና የተቀመጠውን ሥርዓት ቢጥስ አስተማሪ የሆነ ቅጣት በባህላዊ ሥርዓት ይጣልበታል፡፡

ታዲያ ጀፎር የወል ወይም ባለቤትነቱ የሕዝብ በመሆኑ ለሁሉም ሰው መተላለፊያ እና ብዙ አገልግሎቶችን የሚያገኝበት በመሆኑ ለደህንነቱና ለአሠራር ሥርዓት መጠበቅ የአካባቢው ኅብረተሰብ በንቃት ይሳተፋል፡፡

ከብዙ ዘመናት በፊት አባቶች ጠብቀው ያቆዩትና በሀገር በቀል ዕውቀት የተገነባውን ይህንን እሴት ወጣቱ ትልድ በመጠበቅና እሴት በመጨመር ተንከባክቦ ለትውልድ ጥቅም ከማዋልና ከማሻገር አንጻር ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

ይህንን ውብ ሥፍራና በጎ ተሞክሮን ከማስተዋወቅና ለቱሪዝም መስህብ መዳረሻነት ከማዋል ረገድ የሚመለከተው አካል ድርሻውን ከተወጣ እነዘህን የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ጸጋዎችን በመንከባከብ በመጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቀም ማግኘት ይቻላልና፡፡

አዳዲስ የሚመሠረቱ ከተሞችና የቆዩ ከተሞችም ቢሆኑ በተለይ የወል መገልገያ ሥፍራዎችን ከማበጀትና ከመጠበቅ አንጻር የጉራጌ አባቶች ካቆዩልን እሴት ብዙ ትምህርት የሚወሰድበት ነው፡፡

በመሆኑም የዚህ ዓይነትና ሌሎች ተመሣሣይ ጠቃሚ እሴቶችና አወንታዊና ጠቃሚ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ከተሠራ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥ እገዘው ቀላል አይሆንም፡፡

ቸር እንሰንብት!!