ርዕሰ መስተዳድሩ በአማራ ክልል ሰላም ለማፅናት የፀጥታ ኃይሉን የማጠናከር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

የካቲት 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በአማራ ክልል የተገኘውን ሰላም ለማስፋትና ለማጽናት የፀጥታ ኃይሉን በማደራጀትና በማሰልጠን ለቀጣይ ተልዕኮ የማዘጋጀት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው የፀጥታና ወቅታዊ ሁኔታዎችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው እንደገለጹት ቀደም ሲል በፀጥታ ችግር ውስጥ በቆዩ አካባቢዎች አሁን ላይ ሰላም ሰፍኗል።

ይህም የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ አመራር አባላትና ሰላም ወዳዱ ህዝብ ባደረጉት የተቀናጀና የተናበበ ስራ የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በየደረጃው በተካሄዱ ውይይቶች የመንግስትን አቋምና የጥፋት ኃይሉን እኩይ ድርጊት ለህዝብ ግልጽ በመደረጉ ህዝቡ ከመደናገር መውጣቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ይሁን እንጂ ሰላም በአንድ ወገን ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ገልፀዋል።

የሰላም ጥሪ ከማቅረብ ጎን ለጎን የህግ ማስከበር ስራና ሰላምን በዘላቂነት የማጽናት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ መንግስት በማመን በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለዚህም በቅርቡ የተጀመረው የክልሉን የፀጥታ ኃይል በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና በማሰልጠን ለቀጣይ ተልዕኮ የማዘጋጀት ስራ በቀጣይም ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የተጀመሩ ውይይቶችን እስከ ታች ድረስ አጠናክሮ በማስቀጠል ህዝቡን ከመንግስት ጎን የማሰለፍ ስራ የእለት ተእለት ተግባር መሆኑን የምክር ቤት አባላት በመገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ክልሉ ከፀጥታ አኳያ ያሉ ስትራቴጂካዊ የውጭና የውስጥ ስጋቶች ምን እንደሆኑ በመለየትና በመተንተን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ የመከላከል አቅምን ለማዳበር እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሚሰራው ስራም ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመገንባት፣ የህዝቦችን ትስስር ለማስቀጠል፣ የኢትዮጵያን አንድነት ማጽናት በሚያስችል መልኩ የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል።

ትናንት የተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤም በአስፈጻሚ አካሉ ሪፖርትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ተጠናቋል።