የምንዘጋጀው ለጦርነት ሳይሆን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ሉአላዊነት መከበር ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ግንቦት 9/2016 (አዲስ ዋልታ) የምንዘጋጀው ለጦርነት ሳይሆን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ሉአላዊነት መከበር ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ የሞተር ቪሄክልስ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪን እና የመከላከያ የሜንቴናንስ መምሪያን ጎብኝተዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተቋማዊ ወትሮ ዝግጁነታችንን በማረጋገጥ ተመራጭ የሰላም ኃይል ገንብተናል ብለዋል።

መከላከያ ተቋማችን ሀገርን ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመመከት ሰላምና ሉአላዊነቷን እያስጠበቀ በኢንዱስትሪው ዘርፍም በመሳተፍ የራስን አቅም በራስ በመገንባት ሁለንተናዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።

አሁን ላይ የተቋሙን የማድረግ አቅም ከነበረው እጥፍ በማሳደግ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ተቋም መሆን ችለናል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተቋም በሁሉም ዘርፍ አቅምን በማሳደግ ተቋማዊ ግንባታችንን የታለመለት ግብ ላይ ማድረስ እየቻልን ነው ብለዋል።

በጦርነት ውስጥ ሆነን በሁኔታ ሳንበገር የጀመርነውን ተቋማዊ ሪፎርም በሚፈለገው ልክ ውጤታማ በሆነ መልኩ እያስኬድን እንገኛለን ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በጉብኝቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የጦር የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ እና የሚንስቴሩ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጀኔራል መኮንኖች ተገኝተዋል።