በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ከሰሞኑ ያደረጉት ንግግር ከወዳጅ ሀገር የማይጠበቅ ነው – አምባሳደር ነብዩ ተድላ

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳድር ነብዩ ተድላ

ግንቦት 15/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ከሰሞኑን ያደረጉት ንግግር ከወዳጅ ሀገር የማይጠበቅ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ተናገሩ።

አምባሳደር ነብዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ መስጠቱን አስታውስው የአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንደ ሀገር መነጋገር ሲገባቸው ያልተጠየቁትን ምክር ሰጥተዋል ብለዋል።

የሀገራት ወዳጅነት ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ የሚመሰረት ነው ያሉት አምባሳደር ነብዩ የአሜሪካው አምባሳደር መንግስት እንዴት ማስተዳደር እንዳለበት የመናገር መብት የላቸውም ብለዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ ጋር በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍን በተመለከተ ዓለምአቅፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ መምከራቸውን አንስተዋል።

በመስከረም ቸርነት