ፓርቲው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እንዲለወጥ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የያዘውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው- መለስ ዓለሙ

የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ

ግንቦት 17/2016(አዲስ ዋልታ) ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እንዲለወጥ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የያዘውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ መሆኑን የፓርቲው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ ገለጹ።

ፓርቲው አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ የጸና አቋም እንዳለውም ጠቅሰው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ በርካታ እርምጃዎች መውሰዱንም ገልጸዋል።

የመንግስት ስልጣን ሽግግር በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲሆንና ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያከናወነው ስራ ለዴሞክራሲ ባህል መዳበር አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

በፓርቲው የውስጥ ዴሞክራሲን የማጎልበት ስራ፤ የዴሞክራሲ ስርዓትን መገንባትና ማጽናትን ዓላማ የያዘ ነው ብለዋል።
ብልጽግና የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩና ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድም ውጤታማ ስራዎችን መከናወኑን አስረድተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋማዊና ሎጅስቲካዊ አቅም እንዲጠናከር በማድረግ የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብትና የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ከፓርቲዎቹ ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገንም ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ለችግሮች መፍትሄ የሚገኘው በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ ትግል ነው ብሎ እንደሚያምን፣ በኃይል የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ኢትዮጵያና ሕዝቧቿን አይመጥንም ያሉ ሲሆን ማንኛውም ጉዳይ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይትና በሀሳብ የበላይነት ይፈታል ብሎ እንደሚያምንም አብራርተዋል።

ፓርቲው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የያዛቸውን አቋሞች በማጠናከር በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እንዲጎለብት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በአንድ ጀምበር የሚሳካ አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ ሕብረተሰባዊና ተቋማዊ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ አንስተዋል።

ጠንካራ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ መገንባት፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት የሚያግዙ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና ሌሎች የፖለቲካ ባህሉን የሚያሳድጉ አስቻይ ሁኔታዎች መፍጠር ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ሰላማዊ ትግልና የሕግ የበላይነት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ ይህ እንዲሆንም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሳካ ብልጽግና ፓርቲ የማይናወጥ አቋም እንዳለውና በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም መናገራችውን ኢዜአ ዘግቧል።