የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ግንቦት 23/2016 (አዲስ ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የምክር ቤቱ ውሳኔዎች ቀጥለው ቀርበዋል፡-

32ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ አዋጅ ላይ ነው፡፡
ከህጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አልተካተተም፡፡

በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ የአዋጅ ማሸሻያ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠልም ምክር ቤቱ የተወያየው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ላይ ነው፡፡

የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችንና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ፤ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተበታትነው ያሉትን የንብረት ማስመለስ እና አስተዳደር ድንጋጌዎች በአንድ ወጥ ሕግ ውስጥ በማካተት ለአፈጻጸም ምቹ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

3. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አድርጎ ስለማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበው አዋጅ ላይ ነው፡፡

በወንጀል የተገኘን ንብረት ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የደህንነት ስጋት ከመሆኑ በተጨማሪ የፋይናንስ ስርዓቱ የተረጋጋ፣ ግልጸኝነት ያለው፣ ጤናማና ቀልጣፋ እንዳይሆን የሚያደርግ ነው፡፡

ስለሆነም ይህን ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ በቀረበው አዋጅ ላይ ነው፡፡ የነዳጅ ውጤቶች ካላቸዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ አንጻር አቅርቦታቸውን፣ ክምችታቸውን፣ ስርጭታቸውን፣ ዋጋቸውን፣ ጥራታቸዉን እና ደህንነታቸውን መቆጣጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤ እንዲሁም ከአስመጪ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚዎች ድረስ ያለው ግብይት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ፍትሐዊ እና ተደራሽ የሆነ የአቅርቦት ሰንሰለት እና የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡