የሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድር ጀማሪ ዋልታ ነበር – ጋዜጠኛ መሐመድ ሐሰን

የዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሐመድ ሐሰን

የደሞ አዲስ የአሸናፊዎች አሸናፊ የፍፃሜ ውድድር ላይ የዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሐመድ ሐሰን ያደረጉት ሙሉ ንግግር እንደሚከተለው ቀርቧል።

እኛ ደሞ አዲስን ከመጀመራችን በፊት፣ በሀገራችን ከኛ ቀድመው የሙዚቃ ተሰጥዖ ውድድርን መንገድ ጠርገው ያቀኑልንን ብዙ ተመስጋኝ ከያኛንና ውድድሮች ነበሩ፤ አሉም። የብዙዎቻችን የአፍላነት ትዝታ የሆነው የኢትዮጵያን አይዶል ቀደምት አዘጋጆች እነ ይስሃቅ ጌቱና ጀማል መሀመድ ፣ዳኞች የነበሩት እነ መምህር ፈለቀ ሀይሉ፣ እነመምህር አክሊሉ፣ እነሙሉ ገበየሁ… ወዘተ። ከዚያ ደግሞ ኤሊሾ ! የሙዚቃ መልክ! የሙዚቃው ዋርካ! ኤሊያስ መልካ፣ ባላገሩ አይዶልና አብርሃም ወልዴ፣  ሱልጣን ኑሪ፣ እነ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ዳግማዊ ዓሊ   እነ ሰርጸ ፍሬስብሃት፣ እነየሺ ደመላሽ… እነ ስንቱን ዘርዝሬ እዘልቃለሁ? … ብዙ ባለሞያዎችን ያፈራውን ፋና ላምሮትን ጨምሮ ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን ውድድሮችና ያልጠራኋቸውን ከያኒያን ሁሉ ለነበራቸው ሚና ሁሉ በደሞ አዲስ ስም ምስጋና ላቀርብላቸው እወዳለሁ።

ነገር ግን ከላይ ከዘረዘርኳቸው ውድድሮች ሁሉ የሚቀድም ሌላ የሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድር በሀገራችን ነበረ። ታስታውሱ እንደሆን በ1988ዓ.ም አሁን በዋልታ ስር የሚገኘው ሜጋ ኪነጥበባት ያዘጋጀው አንድ የሙዚቃ ዉድድር የብዙዎቻችንን ቀልብ ስቦ ነበር። አበበ ተካ “ሰዉ ጥሩ “በሚለዉ ሙዚቃዉ፣ ዮዲት ዘለቀ “ጎዳና ነዉ ቤቴ” በሚል ሙዚቃዋ  ከሌሎች 150 ተወዳዳሪዎች ጋር የተወዳድሩበት። በውድድሩም አበበ ተካ አንደኛ ዮዲት ደግሞ ሁለተኛ ወጥታ ነበር። በኔ ግምት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ውድድር የተካሄድው ያኔ ነው። የታሪኩ ባለቤትም በሜጋ በኩል የኛው ተቋም ዋልታ እና በወቅቱ የነበሩት ባለሞያዎች ናቸው። ይህንን ነው ከላይ የጅማሬ ታሪክ ያልኩት።

ታዲያ ይሄንን ያነሳሁት … ቀደምት እኛ ነበርን ለሚል ትምክህትና የታሪክ ሽሚያ አይደለም። በኛ ውስጥ የሀገራችንን የኢትዮጵያን መልክ ለማሳየት ነው። ኢትዮጵያ ቀደምት የሚባል የስልጣኔ ታሪክ እና የተከማቹ ቅርሶች ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ልክ የዋልታው ሜጋ የቀደመ የተሰጥዖ ውድድር ታሪክና የተከማቸ አርካይቭ እንዳለው ሁሉ። ነገር ግን በቅርሶቻችን ብቻ እየተኩራራን የምንኖርበት ዘመን አብቅቷል። የታሪክ ረዣዥም እግሮቻችን ከዘመናችን ክንፋሞች እኩል ሊያስመነጥቁን አይችሉም። ከነበረው ተምረን ለራሳችን አዲስ ታሪክ ካልፃፍን በቀር አወዳደቃችን የከፋ ይሆናል። ስለዚህ ልክ እንደምንወዳት ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ታሪካችንን ለጎብኚ አመቻችተን የራሳችንን አዲስ ጉዞ ጀመርን።