የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች በትብብር ለመስራት የሚያስችል ውይይት አካሄዱ

ግንቦት 27/2016 (አዲስ ዋልታ) የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሐመድ ሐሰን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ሁለቱ ተቋማቱ በጋር ሊሰሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

ኃላፊዎቹ የየተቋማቱን ተሞክሮዎች፣ ራዕዮች፣ የሰው ኃይል፣ የስራ ከባቢን፣ የሀብት አጠቃቀም እና መሰል ጉዳዮችን አንስተው ምክክር አድርገዋል፡፡

በምክክሩ ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን ጠንካራ አቅም በማቀናጀት መስራታቸው የላቀ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችላቸው ተነስቷል፡፡

የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሐመድ ሐሰን ሁለቱ ተቋማት ለአገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው በትብብር መስራታቸው የበለጠ ውጤታማ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው ተቋማቸው የራሱን ሚዲያ ለማቋቋም አስቦ የነበረ ቢሆንም ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ካለው ሰፊ ባለሙያና ልምድ አንጻር በትብብር መስራቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም ሁለቱ ተቋማት በትብብር ሊሰሩ የሚችሉበት ህጋዊ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡

ከምክክሩ በኋላ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ እና የስራ ባለደረቦቻቸው የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት መስሪያ ቤትን ጎብኝተዋል፡፡