የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎችን የያዘ መጽሐፍ ይፋ ሆነ


ሰኔ 4/2016 (አዲስ ዋልታ) በዛሬው ዕለት ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም የተላለፉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎችን የያዘ መጽሐፍ ይፋ ሆነ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰብሳቢነት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ100 ቀናት ግምገማ ቁልፍ የሆኑ ሴክተሮችን አፈፃፀም በጥልቀት በመመልከት ማካሄድ ጀምሯል።

ከግምገማ መድረኩ በተጓዳኝ ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም የተላለፉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎችን የያዘ መጽሐፍ ይፋ ሆኗል።

መጽሐፉ በተጠቀሰው ዘመን የተላለፉ የፖሊሲ ውሳኔዎችን በዝርዝር ያመለክታል ነው የተባለው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ክፍል የሚያከናወነው የመሰነድ ተግባር አንዱ የሆነው ይህ መጽሐፍ ለታሪክ ስነዳ እና መረጃውን ለሚሹ ሁሉ ጠቃሚ የሆነ የሰነድ ዝግጅት ስራ አካል መሆኑም ተገልጿል።

የመጽሐፉ ውስን ቅጂዎች ለፌደራል እና ለክልል ተቋማት የሚሰራጩ ሲሆን መረጃውን ለሚፈልጉ ሁሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረገጽ ላይ እንደሚጫን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡