ም/ጠ/ሚኒስትሩ በ850 ሚሊዮን ብር የተገዙ ዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖችን ስራ አስጀመሩ

ሰኔ 8/2016 (አዲስ ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በ850 ሚሊዮን ብር የተገዙ አምስት ዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖች (ኤር ትራክተርስ) በይፋ ስራ አስጀመሩ።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝና ሌሎች አደጋዎችን ለመቆጣጠር የራሷ የኬሚካል ርጭት አውሮፕላኖች ስላልነበራት ለኪራይ እስከ 13 ቢሊየን ብር ወጪ ስታደርግ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የአደጋ መቆጣጠሪያ የኬሚካል ርጭት አውሮፕላኖች እንዲኖራት ይደረጋል ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ይህን ተከትሎም መንግሥት አምስት ዘመናዊ የኬሚካል ርጭትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊ ኤር ትራክተሮችን ግዥ ፈጽሞ በዛሬው ዕለት በይፋ ስራ አስጀምሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት ከዚህ ቀደም የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የደን ቃጠሎና የግሪሳ ወፍን መቆጣጠር የሚያስችል ሀገራዊ አቅም ባለመኖሩ በሰው ኃይል በባህላዊ መንገድ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።

በሰሜን ተራሮችና በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ቃጠሎ ባጋጠመ ጊዜ ኢትዮጵያ በልመና እና በኪራይ ከሌሎች አገራት የርጭት አውሮፕላኖችን በማምጣት ስትጠቀም መቆየቷን አውስተዋል።

አሁን ላይ መንግስት አደጋን በራስ የመቋቋምና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አካል ያደረገውን የአምስት ኤር ትራክተሮች (የርጭት አውሮፕላኖችን) ገዝቶ ወደ ስራ ማስገባቱንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በማስጀመሪያ መርኃግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የናሽናል ኤር ዌይስ አመራሮች ተገኝተዋል።