የኢትዮጵያና የሩሲያ የመንግስት ለመንግስትና የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል


ሰኔ 9/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያና የሩሲያ የመንግስት ለመንግስትና የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የልዑክ ቡድን ከሰኔ 9 እስከ 12/2016 በሚካሔደውና ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር በሚል መሪ ቃል በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።

ከፎረሙ ጎን ለጎንም አቶ አደም ፋራህ ከሩሲያ ዩናይትድ ፓርቲ ምክትል የጽሕፈት ቤት ሃላፊ ክሊኖቭ አንድሬ ጋር ተወያይተዋል።

አቶ አደም በውይይታቸው ላይ በኢትዮጵያና በሩሲያን መካከል ያለውን ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት ያነሱ ሲሆን ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ችግሮች ሲገጥሟት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን ላሳየችው ድጋፍና ወዳጅነት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ያነሱት አቶ አደም ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ባደረገችው ጥረትም ሩሲያ ላደረገችው ድጋፍ የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲንና መንግስቱን አመስግነዋል።

ቀደም ሲል በሁለቱ ሃገራት የነበሩ የመንግስት ለመንግስትም ሆነ የፓርቲ ለፓርቲ ትብብሮች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደሚደረግም አቶ አደም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሃገር እንደመሆኗም የሩሲያ ባለሃብቶች በመምጣት በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩም ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ቡና፣ አበባ፣ ሰሊጥ ጥራጥሬ እና ሌሎች የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በቀጥታ ወደ ሩሲያ ገበያ ለመላክ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸውላቸዋል።

የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም የሩሲያ ባለሃብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም ግብዣ አድርገውላቸዋል።

የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ምክትል የጽሕፈት ቤት ሃላፊ ክሊኖቭ አንድሬ በበኩላቸው በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር የፓርቲያቸው ፍላጎት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሩሲያና ኢትዮጵያ በሁሉም ጊዜ የማይለዋወጥ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው ይሄንንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አዲስ የብሪክስ አባል ሃገር ሆና በመቀላቀሏም እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት ምክትል የጽህፈት ቤት ሃላፊው በቀጣይ ዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በተለያዩ የትብብር መስኮች ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።