የአዲስ ዋልታ ባልደረባ ሊዲያ ኪታሞ ስርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት ተፈጸመ

ሊዲያ ኪታሞ

የዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ባልደረባ ሊዲያ ኪታሞ ስርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት በማሻ ሀመረ ኖህ ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።

ሊዲያ ኪታሞ ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ በትላትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

ከመጋቢት 13/2014 ዓ.ም ጀምሮ በዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት የስቱዲዮ ካሜራ ባለሙያ ሆና ያገለገለችው ሊዲያ ኪታሞ ከአባቷ ከአቶ ኪታሞ ጋውሰራሻ እና ከእናቷ ከወይዘሮ ተዋበች አየለ በሐምሌ 22/1981 ዓ.ም ተወልዳ በ 35 ዓመቷ ከዚህ ዓለም ድካም አርፋለች።

ህይወቷ እስኪያልፍ በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት የስቱዲዮ ካሜራ ባለሙያ በመሆን ያገለገለችው ሊዲያ በሸካ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን እንዲሁም በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በካሜራ ባለሙያነት በቅንነትና ታታሪ በመሆን አገልግላለች። ሊዲያ ኪታሞ ባለትዳርና የአንድት ሴት ልጅ እናት ነበረች።

ዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ለቤተሰቦቿና ወዳጅ ዘመዶቿ መጽናናትን ይመኛል።