የዊክሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጅ ከእስር ተለቀቀ

ጁሊያን አሳንጅ

ሰኔ 18/2016 (አዲስ ዋልታ) ለረጅም ዓመታት ከቆየ የፍርድ ቤት ሙግት በኋላ የ52 ዓመቱ የዊክሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጅ ከአሜሪካ ጋር በተደረገ ስምምነት ከእስር ተፈቶ ከብሪታኒያ ወደ አሜሪካ አቅንቷል።

ከአስር ዓመት በላይ በእስር የቆየው አውስትራሊያዊው ጁሊያን አሳንጅ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በሚስጢር የያዟቸውን ሰነዶች ለዓለም ይፋ በማድረግ ይታወቃል።

አሳንጅ አሜሪካ ካቀረበችበት 18 ክሶች መካከል “የአሜሪካን ሚስጢራዊ መረጃዎች ለመመንተፍ ማሴርና ይፋ ማድረግ” የሚለውን ክስ ለማመን በመስማማት ነው ከእስር ሊፈታ የቻለው፡፡

በብሪታንያ በእስር ያሳለፋቸው ዓመታት ከግምት ውስጥ በማስገባት በአሜሪካ ምንም አይነት የእስር ጊዜ እንደማይኖረው የአሜሪካው ሲቢኤስ አስነብቧል፡፡

ስለኢራቅ እና አፍጋኒስታን ጦርነቶች መረጃን ይፋ ያደረጉት የዊኪሊክስ ፋይሎች የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥለዋል ስትል አሜሪካ አሳንጅን “የአገሪቱ የመከላከያ ሚስጢራዊ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል” በሚል ነበር ክስ የመሰረተችው፡፡

የዊክሊክስ የመረጃ ምንተፋ “በአሜሪካ መከላከያ ታሪክ ውስጥ ከተፈጸሙት የሚስጥራዊ ሰነዶች ስርቆት መካከል ትልቅ ከሚባሉት አንዱ ነው” ስትል የገለጸችው ዋሽንግተን ብሪቴይን ጋዜጠኛውን አሳልፋ እንድትሰጣት ስትጠይቅ መቆየቷ ይታወሳል፡፡

የአሜሪካ ተላልፎ ይሰጠኝ ጥያቄና ክስ ጋዜጠኝነት የሚያዋርድና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚቃረን ነው የሚሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልቤንዝ የ52 ዓመቱ ጋዜጠኛ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ዊክሊክስ እ.ኤ.አ በ2010 በባግዳድ ሁለት የሮይተርስ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከአስር በላይ የሚሆኑ ሲቪል ኢራቃዊያን ሲገደሉ የሚያሳይ ከአሜሪካ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ላይ የተቀረጸ ቪዲዮ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የሀገራትን ሚስጢራዊ መረጃ በማውጣት ከ10 ዓመት በላይ በእስርና ክርክር ውስጥ የቆየው ጁሊያን አሳንጅ በነገው ዕለት በነፃነት ወደ አውስትራሊያ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡