በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ተካሄደ


ሰኔ 20/2016 (አዲስ ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በቄለም ወለጋ ዞን ላሎ ቂሌ ወረዳ በመገኘት የ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አስጀመሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ መንግስት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከአየር ንብረት ለውጥና መዛባት ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል እንዲሁም የአፈር መሸርሸርና የውሃ እጥበትን ለመቀነስ ለአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝና በዚህም ክልሉ ቀዳሚውን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት እንደ ክልል በአጠቃላይ ለማዘጋጀት ካቀድነው 5.5 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ ወደ 5 ቢሊዮን የሚጠጋ የደረሰ ችግኝ የመትከል ሥራ የተጀመረ መሆኑን እንዲሁም የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችም ሙሉ በሙሉ መዘጋከታቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ አመልክተዋል፡፡

በዚህ ዓመት በችግኝ እንሸፍነዋለን ብለን ካቀድነው 1.29 ሚሊዮን ሄክራት መሬት ውስጥ 814 ሺሕ ሄክታር መሬት ከሳተላይት ምስል ጋር የተናበበ (geo-referenced) እንዲሆን መደረጉን ጠቁመው ከሚተከለው ችግኝ ውስጥ 10 በመቶው የተለያዩ ለምግብ የሚውሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በድምሩ 18 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞችን የተተከለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 88.5 በመቶው ፀድቋልም የተባለው።

በዚህም ከ2011 ዓ.ም በፊት 17 በመቶ የነበረውን የክልላችን የደን ሽፋን ወደ 27 በመቶ አካባቢ ማሳደግ የተቻለ ሲሆን በአጠቃላይ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በምናደርገው ጥረት ውስጥ፣ የክልላችን ህዝብ እየተወጣ ላላው ግንባር ቀደም ሚና ያለኝን ከፍተኛ አድናቆት በራሴና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስም ለመግለፅ እወዳለሁ ብለዋል፡፡