ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት 11ኛ ቅርንጫፉን አስመረቀ


ሰኔ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጣፎ አደባባይ አካባቢ 11ኛ ሱፐር ማርኬቱን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

ዛሬ ያስመረቀው ቅርንጫፍ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከሰሚት ቀጥሎ ሁለተኛው ሲሆን በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ በ2012 በተደረገ የአመራር ለውጥ ኩዊንስ በከፍተኛ የእድገት እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ገበያን ማረጋጋት ዋነኛ ተልዕኳችን ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው አብዛኛው ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በሚድሮክ የተመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ስራዎች ለመስራት በማሰብ በራሳችን እርሻ ላይ የምናመርተውን ምርት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ላሉ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራን ነውም ብለዋል።

በቀጣይም በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች እና በክልል ከተሞች ሱፐርማርኬቱን የማስፋፋት እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታረቀኝ ገመቹ በበኩላቸው የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እያደረገ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ አንስተው በተለይም በተመጣጣኝ ዋጋ ዝቅተኛውን ማህበረሰብ ፍላጎት ለማርካት እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

ክፍለ ከተማው በማንኛውም ሁኔታ እና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም ገልጸዋል።

በሚድሮክ ኢትዮጵያ ስር ያለው ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች 11 ቅርንጫፎች ሲኖሩት ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሆነ የስራ እድልን ፈጥሯል።

በሔለን ታደሰ