40 በመቶ የፋብሪካ ምርቶች በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተመርተው መጠቀም ጀምረናል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሰኔ 27/2016 (አዲስ ዋልታ) 40 በመቶ የፋብሪካ ምርቶች በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተመርተው መጠቀም ጀምረናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 36ኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ቀውሶች ተቋቁማ እና ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር በሁሉም መስኮች አስደማሚ ስኬት አስመዝግባለች ብለዋል፡፡

የእዳ ጫናን ለማቃለልም ከፍተኛ ስራ መከናወኑን ገልጸው አሁን ላይ ያለብንን የእዳ ጫና ከአገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ወደ 17 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ይህንን አሃዝ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ባለፉት 11 ወራት መንግስት 466 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም አንስተው ይህም ከተያዘው እቅድ አንጻር የ96 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ይህ ከኢትዮጵያ አገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር 7 በመቶ ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህም ከፍተኛ የሆነ ግብር መሰወር መኖሩን አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ በመሆኑ ይህንን ጥረትም ዜጎች ሊያግዙ ይገባል ብለዋል፡፡

ከችግሮች ውስጥ እድሎችን ፈልቅቀን በማውጣት ስኬታማ ዓመት አሳልፈናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማብራሪያቸው አንስተዋል።

ስንዴን ጨምሮ በተኪ ምርቶች ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በማብራሪያቸው በበጀት ዓመቱ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከምርትና አገልግሎት ወጪ ንግድ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም አንስተዋል፡፡

ከሐዋላ አገልግሎትም 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም በምስራቅ አፍሪካ ትልቋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሳቢ አገር መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበጀት ዓመቱም 3 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ እንደቻለች ገልጸዋል፡፡

የ2016 ዓ.ም የገቢ ዕቅድ 529 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን በ11 ወራት ውስጥ 466 ቢሊዮን ብር (96 በመቶ) ቢሊዮን ብር ሰብስበናል ሲሉም ገልጸዋል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን አንስተዋል።

ወጭን በተመለከተ 730 ቢሊዮን ብር ወጭ የታቀደ ሲሆን 716 ቢሊዮን ብር (98 በመቶ) በ11 ወራት ውስጥ ተመዝግቧል።