ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ


ሐምሌ 9/2016 (አዲስ ዋልታ) በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ከ298 ሺሕ ቶን በላይ ቡና 1 ነጥብ 43 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ጥራት ያለው የቡና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ 298 ሺሕ 500 ቶን የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ገልጸው ለውጭ ገበያ የተላከው የቡና ምርት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ50 ሺሕ 500 ቶን ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

በዓመቱ ለውጭ ገበያ የተላከው የቡና ምርት በጥራትና በመጠን ከፍተኛ እንደነበርም አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ ያመረተውን የቡና ምርት የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር በቀጥታ ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ ማድረግ መቻሉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በበጀት ዓመቱ አርሶ አደሩ ከቡና ምርት የሚያገኘውን ገቢ ከ40 በመቶ ወደ 80 በመቶ ማሳደግ መቻሉም ተገልጿል።