ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በድርሀም እና በብር ሊገበያዩ ነው


ሐምሌ 9/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ለመጠቀም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዢ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ መፈረማቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ባንኮቹ ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶችን ለመፈጸም፣ የክፍያ እና የመልእክት መላላኪያ ስርዓቶቻቸውን ለማስተሳሰር የሀገር ውስጥ ገንዘቦችን ለመጠቀም የሚያስችል ማዕቀፍ ለመዘርጋት ሁለት የመግባቢያ ሰነዶች መፈራረማቸውም ነው የተገለጸው።

የመጀመሪያው ስምምነት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ እና የኢትየጵያ ብሔራዊ ባንክ እስከ 3 ቢሊዮን ድርሃም እና 46 ቢሊዮን ብር የሚደርሱ የሀገር ውስጥ ገንዘቦችን እንዲለዋወጡ ያስችላቸዋል ተብሏል።

በተጨማሪም በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የገንዘብ እና የንግድ ትብብር በአገር ውስጥ ምንዛሬዎች ለፋይናንሺያል ገበያ በማቅረብ ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶችን የበለጠ ውጤታማ እና ቀልጣፋ እልባት እንዲያገኙ ያስችላል።

ሁለተኛው የመግባቢያ ስምምነት ባንኮቹ የፈጣን ክፍያ ስርዓታቸውን፣ የብሄራዊ ካርድ መቀየሪያዎችን UAESWITCH እና ETHSWITCH እንዲሁም የመልእክት መላላኪያ ስርዓቶችን በእያንዳንዱ ሀገር የቁጥጥር ስርዓት መሰረት በማገናኘት በክፍያ መድረክ አገልግሎቶች እና በኤሌክትሮኒክ የክፍያ ዘዴዎች ዙሪያ ተባብረው ለመስራት የሚያስችል ነው፡፡

በዚህም በሁለቱ ሀገራት ለሚደረግ ግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ማለትም ድርሃምና ብር ለመጠቀም ከስምምነት የደረሱ ሲሆን ሁለቱ አካላት ለተግባራዊነቱ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ጥረት እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የኢትዮጵያ አንዷ የንግድ አጋርና የውጪ ኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኛን ገልጸው ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርገዋል ብለዋል።

በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረት ቀጣይነት ያለው ልማትና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዥ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ መምጣታቸውን እንደሚያሳይ አመላክተዋል።