የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት 230 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ


ሐምሌ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት 230 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ከተመደበው በጀት ውስጥ 146.48 ቢሊዮን ብር (63.6%) ለካፒታል እንዲሁም 74.55 ቢሊዮን ብር (33.4%) ለመደበኛ ወይም ለአስተዳደርዊ ወጪ የተመደበ መሆኑን ገልጸዋል።

ለካፒታል ከተመደበው ውስጥ 90.4 % ለድህነት ቅነሳ እና እድገት ተኮር ዘላቂ ልማት ለሆኑ ፕሮጀክቶች የተመደበ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ውድ የከተማችን ግብር ከፋዮች፤ ይህን በጀት ማሳካት የጋራ ርብርብ ይጠይቃል ያሉት ከንቲባዋ በ2016 በጀት ዓመት ግብራችሁን በወቅቱ በፈቃደኝነት በመክፈላችሁ 146.8 ቢሊዮን ብር ግብር ሰብስበን 18,091 ፕሮጀክቶችን እና የኮሪደር ልማትን ተግብረን ከተማችንን እንደ ስሟ ውብ አበባ በማድረግ የጋራ አሻራችንን እያስቀመጥን ነው ብለዋል።

በዚህ ዓመትም እጅ ለእጅ ተያይዘን የበለጠ ለመስራት ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ ሲሉም አክለዋል።