310 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መላኩን የጋንቤላ ክልል አስታወቀ

ተንኩዌይ ጆክ

ሐምሌ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ 310 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መላኩን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ተንኩዌይ ጆክ ተናገሩ።

በክልሉ የተቋቋመው የማዕድን ኮማንድ ፖስት የ12 ወራት የሥራ ክንውኑን ገምግሟል።

በአፈፃፀም ግምገማ ላይ ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የማዕድን ዘርፉ ላይ እየተደረገ ያለው ቁጥጥርና ክትትል አበረታች መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ወደ ብሔራዊ ባንክ እየገባ ያለው መጠን እየተሻሻለ ቢሆንም በክልሉ ያለውን የወርቅ ሀብት ቁጥጥር በማጠናከር ለብሔራዊ ባንክ የሚገባውን መጠን ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አዳዲስ ወርቅ አምራች ማኀበራት ፍቃድ ወስደው ለ2 ሺሕ 404 ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩም በግምገማው ላይ ቀርቧል።

የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኃላፊ አኳታ ቻም በበኩላቸው ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ ምርት ለማሳደግ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎችን እያሰፋን እንገኛልን ብለዋል።

የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያሳየው የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለማስቀረት ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ጋር በመናበብ የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።