ከ7 ሺሕ በላይ ከባድ ወንጀል የፈጸሙ አካላት እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል – ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው

ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው

ሐምሌ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ፖሊስ በወሰዳቸው እርምጃዎች 7 ሺሕ 405 ከባድ እና ከ26 ሺሕ በላይ መካከለኛ ወንጀል የፈጸሙ አካላት እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገለጹ።

ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በጠንካራ የወንጀል መከላከል ሥራ የህዝብ የዕለት ተዕለት እንቅሰቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ከባድ ወንጀሎችን 31 በመቶ መቀነስ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በጀት ዓመቱ የወንጀል መከላከል እንዲሁም ሰላምና ደኅንነትን የማስጠበቅ ተቋማዊ አቅምን ማጎልበት የሚያስችል ስኬታማ የለውጥ እርምጃ መወሰዱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ የአደባባይ በዓላትንና ስፖርታዊ ክዋኔዎችን በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ የተቻለበት ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አንስተዋል።

ኮሚሽነሩ በኦፕሬሽን ስራዎች ወንጀል የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ከ13 ሺሕ በላይ መዛግብት ተደራጅተው ለዓቃቢ ሕግ መላካቸውንም አንስተዋል።

አደንዛዥ እፆችን ሲጠቀሙና ሲያስጠቅሙ እንዲሁም ቁማር ሲያጫውቱ የተገኙ አካላት ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋልም ብለዋል፡፡

በጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደው እርምጃም በሀገር ላይ ሊደርስ የነበረን ከፍተኛ አደጋ መቀልበስ የተቻለበት ስኬታማ ሥራ መሰራቱን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገልጸዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ሚሊኒየም አካባቢ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 38 የፅንፈኛ ቡድን አባላትን ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡