ርዕሰ መስተዳድሩ በብልሹ አሰራር ውስጥ የገቡ 196 አመራሮችን ከኃላፊነት መነሳታቸውን አስታወቁ


ሐምሌ 5/2016 (አዲስ ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መልካም አስተዳደርን ከማስፈንና እንጻር ብልሹ አሰራር ውስጥ የገቡ 196 አመራሮችን ከኃላፊነት መነሳታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያስታወቁት የክልሉ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በበጀት ዓመቱ ክረምት ተከላ ወቅት 129 ሚሊዮን 102 ሺሕ 135 ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው በአንድ ጀንበር 20 ሚሊዮን 512 ሺሕ 583 ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰዋል።

በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ 1 ሺሕ 73 ንዑስ ተፋሰስ ላይ 217 ሺሕ 384 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉንም የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በበጀት ዓመቱ በበልግና በመኸር 80 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በመኸር እና በበልግ በዋና ዋና የአዝርዕት ሰብሎች 688 ሺሕ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን እና 19 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸው በግብዓት አቅርቦትም በኩል 190 ሺሕ 13 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት መካሄዱን በሪፖርት ማንሳታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

በክልሉ በሌማት ትሩፋት ጥሩ አፈጻጸም መኖሩን ጠቅሰው 266 የወተት መንደሮች፣ 447 የዶሮ መንደሮች፣ 977 የንብ ሀብት መንደሮች እና 73 የዓሳ ግብርና መንደሮች መደራጀታቸውን ተናግረዋል።

1 ሚሊዮን 915 ሺሕ 110 የአንድ ቀን ጫጩት እንዲሁም 2.7 ሚሊየን ቀብና ኮክኔ መሰራጨቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ከ70 ሺሕ ቶን በላይ የማር ምርት ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል።

የተቀናጀ የገቢ አሰባሰብና አስተዳደር ሥርዓትን በመከተል በበጀት ዓመቱ ከ5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ላይ ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን ከ95 በመቶ በላይ መፈፀም መቻሉን አመልክተዋል፡፡

ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በተደረገ ጥረት በበጀት ዓመቱ 16 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 41 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በግብርናና ኢንዱስትሪ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ለ64 ሺሕ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩንም ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።