የኢትዮጵያ አየር መንገድ 405 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ


ሐምሌ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2016 የበጀት ዓመት 405 ቢሊዮን ብር (7 ነጥብ 02 ቢሊዮን ዶላር) ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የአየር መንገዱን የ2016 አፈጻጸም የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ ከተገኘው 7 ነጥብ 02 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ ከመንገደኞች ማጓጓዝ 5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከጭነት ደግሞ 1 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል።

በ2016 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ አየር መንገድ 17 ነጥብ 1 ሚሊዮን መንገደኞችን ያጓጓዘ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑት አለማቀፍ እንዲሁም 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የሀገር ውጥ ተጓዦች መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

577 ሺሕ 746 የበረራ ሰዓትን የበረረ ሲሆን ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የበረራ ሰዓት የ19 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደንበኞቹን ፍላጎት ለሟሟላት በበጀት ዓመቱ የበረራ መዳረሻዎችን አስፍቶ በአለም አቀፍ ደረጃ 5 መዳረሻዎች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ወደ 3 ከተሞች በረራ መጀመሩን አቶ መስፍን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ የአየር መንገዱን መዳረሻ ወደ 139 ከፍ ሲያደርግ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹን ደግሞ 22 ማድረሱን አስታውቀዋል።

አየር መንገዱ 754 ሺሕ 681 ቶን ካርጎ ሲያጓጉዝ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ6 በመቶ ብልጫ ማሳዬቱን በመግጫው ተጠቅሷል።

አገልግሎትን በማስፋፋትና በማዘመን በኩልም የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸው የተገለፀ ሲሆን የጥገና፣ የአየር ማረፊያ ማስፋፊያ፣ የአውሮፕላን ግዥና ሌሎች ስራዎች መሰራታቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል።

አየር መንዱድ በቀጣይ 125 አውሮፕላኖችን ማዘዙን የጠቀሱት አቶ መስፍን የቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፊያም እየተጨናነቀ በመሆኑ በቢሾፍቱ አዲስ አየር ማረፊያ በ18 ወራት ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

በቤዛዊት አበበ