የወርቅ ዋጋ በየዕለቱ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሪ ተመን ተባዝቶ እንደሚተመን ተገለጸ

ሐምሌ 24/2016 (አዲስ ዋልታ) የወርቅ ዋጋ በየዕለቱ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሪ ተመን ተባዝቶ እንደሚተመን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ባንኩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ለማንኛዉም ወርቅ አቅራቢ ክፍያ የሚፈጸመዉ የእለቱን ዓለም ዓቀፍ የወርቅ ዋጋ በእለቱ ባንኩ በሚያወጣዉ የዉጭ ምንዛሪ ተመን ተባዝቶ እንደሚሆን ገልጿል፡፡

ባንኩ ወርቅን ከአምራቾችና አቅራቢዎች በብቸኝነት እንደሚገዛ እና የሚገዛበትንም ዋጋ በየግዜዉ በመለዋወጥ አቅራቢዎችን እንደሚያበረታታ ገልጿል፡፡

ስለሆነም ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ጀምሮ በዉጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ላይ ለዉጥ በማድረግ በገበያ የሚመራ የፖሊሲ ማእቀፍን ስለሚከተል ለማንኛዉም ወርቅ አቅራቢ ክፍያ የሚፈጸመዉ የእለቱን ዓለም ዓቀፍ የወርቅ ዋጋ በእለቱ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣዉ የዉጭ ምንዛሪ ተመን ተባዝቶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ወርቅ አምራቾችና አቅራቢዎች ይህንኑ አውቀው የእለቱን የዉጭ ምንዛሪ ተመን ከብሔራዊ ባንክ ድረ-ገጽ ላይ በማገኘት ለሚያቀርቡት ወርቅ ክፍያዉን ወርቁን ከሸጡበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በእለቱ ማግኘት እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡