ሱፍሌ የብቅል አምራች ኩባንያ ኢንቨስትመንቱን እንዲያስፋፋ ድጋፍ እናደርጋለን – ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር)

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር)


ነሐሴ 2/2016 (አዲስ ዋልታ) በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው ሱፍሌ የብቅል አምራች ኩባንያ ያለውን ኢንቨስትመንት እንዲያስፋፋ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይህን የገለፁት ከሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ቶማስ ኔቪው ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።

በውይይታቸውም ኩባንያው ስላለበት ወቅታዊ የምርት ሂደት፣ ተኪ ምርትን ስለማሳደግና ስለ ኤክስፖርት እንዲሁም ስለ ቀጣይ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኩባንያው ኢትዮጵያ የቢራ ገብስ ብቅልን በአጭር ጊዜ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ላደረገችው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱንና እንደ ኬንያ ላሉ ለምርቱ ከፍተኛ ፍላጎት ላላቸው ሀገራት ኤክስፖርት ማድረግ መጀመር እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወሰደው ተጨማሪ የ2 ሄክታር መሬት ላይ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያውን እንዲጀምር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግለት ማረጋገጣቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ እውቅ የፈረንሳይ የቢራ ገብስ ብቅል አምራች ሲሆን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ፈሰስ በማድረግ ኢትዮጵያ ከውጪ ታስገባው የነበረውን የቢራ ገብስ ብቅል ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ በመተካት በኩል ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ከ110 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል አርሲና ባሌ ዞኖች ለሚገኙ ከ60 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የቢራ ገብስ አብቃይ ገበሬዎች ዘላቂ ገበያ የፈጠረ ኩባንያ ነው።