ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሥራ ፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል ጀመረ

ባንኩ ያወጣው መግለጫ



ነሐሴ 2/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሥራ ፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል ጀመሩን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ጀምሮ ሥራ ላይ በዋለው የውጭ ምንዛሪ መመሪያ ቁ.01/2016 መሠረት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት የሚፈልጉ የሥራ ፈቃድ ማመልከቻ እንዲያቀርቡ ጥሪ ያደርጋል፡፡

በገበያ ላይ ተመሥርተው የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መሸጥና መግዛት የሚፈልጉ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲቋቋሙ በተፈቀደው መሠረት የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ እንዲሁም የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ ቢሮ መስፈርቱን አሟልተው ከብሔራዊ ባንክፍቃድ ሲያገኙ መክፈት ይችላሉ፡፡

የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመከፈት የሚያስፈልገው የካፒታል መጠን እንዲሁም ሌሎች ለሥራው የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ከላይ በተጠቀሰው የውጭ ምንዛሪ መመሪያ አባሪ 5 ላይ በግልጽ የሰፈሩ በመሆኑ ከባንኩ ድረ ገጽ ማውረድ እንደሚቻል ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መቋቋም የውጭ ምንዛሪ ገበያን መሠረት ለማስፋትና ለማጠናከር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ ለመሸጥም ሆነ ለመግዛት የሚሹ ደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት እንደሚረዳ እሙን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ባስተላለፉት መልእክት፣ ” የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲከፈቱ የሥራ ፈቃድ መስጠታችን የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ለመክፈትና ዘርፉን በቀጣይ ዓመታት ከዓለም ምርጥ ተሞክሮዎችና አሠራሮች ጋር የተመጣጣነናተወዳዳሪ ለማድረግ የጀመርነውን አዲስ ምዕራፍና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጀመረውን ስትራቴጂካዊ ለውጥ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት መነሣሣቱን የሚያመለክት ነው” ብለዋል፡፡