በሐምሌ ወር ከቡና ወጪ ንግድ ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ


ነሐሴ 4/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ብቻ ወደ ውጭ አገራት ከላከችው ቡና 180 ሚሊዮን 450 ሺሕ ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ54 ነጥብ 29 ሚሊዮን ዶላር (43 በመቶ) እንደሚበልጥ ተመላክቷል።

ገቢው የተገኘው ወደ ተለያዩ አገራት ከተላከው 40 ሺሕ 531 ቶን ቡና ሲሆን የተላከውም መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ17 ሺህ 758 ቶን ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት 298 ሺሕ 500 ቶን ቡና ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ይታወሳል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ወደ 65 አገራት ቡና መላኩ ተጠቁሟል።

ሳዑዲ አረቢያ፣ አሜሪካ፣ ቤልጂየም፣ ጀርመን፣ ቻይና፣ ጃፓንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ከላከችባቸው አገራት መካከል በዋናነት እንደሚጠቀሱ የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል።

በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ከቡና ወጪ ንግድ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱም ተገልጿል፡፡