ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደቱን በስኬት ለማጠናቀቅ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ

ነሐሴ 6/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደቱን በስኬት ለማጠናቀቅ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ።

ኮሚሽኑ በድሬዳዋ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ዛሬ በይፋ የጀመረ ሲሆን በአጀንዳ የማሰባሰብ ላይ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ገጠርና ከተማ 13 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ1 ሺሕ በላይ የህብረተሰብ ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ ላይ ኮሚሽኑ ሀገራዊውን የምክክር ሂደት በስኬት ለማጠናቀቅ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የሀገራዊው ምክክር ሂደቱ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነውን እና ለሀገር ዘላቂ ጥቅም እና አንድነት የሚበጁ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍን በማካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የህዝብ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋሉ የሚሏቸውን መሠረታዊ አጀንዳዎች የሚሰበሰቡበት ምክክር በይፋ መጀመሩን አውስተዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ የመረጣቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ወክለው የተገኙ ወኪሎች እና ባለድርሻ አካላት በነፃነት፣ በእኩልነት እና በመደማመጥ ለአገራዊው ምክክር የሚጠቅሙ መሠረታዊ አጀንዳዎች የሚያቀርቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በመመካከርና በመወያየት የማይፈታ አንዳች ጉዳይ እንደሌለ ያስታወሱት ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ በዚህ በሰለጠነ መንገድ ተነጋግረንና ተወያይተን ኢትዮጵያን አፅንተን እናቆማለን ብለዋል።

በመሆኑም በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ የሚሳተፉ አካላት በትኩረት በነፃነት እና በመደማመጥ ታላቁን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዛሬ በድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ለሚቀጥሉት ሰባት ቀናት የሚካሄድ መሆኑንም የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ላይ ከአስተዳደሩ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ወኪሎች፣ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ተወካዮች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተመካክረው የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን ያዘጋጃሉ።