አየር መንገዱ ከሙምባይ ወደ አዲስ አበባ ለመብረር ሲዘጋጅ በነበረው አውሮፕላን ላይ ስላጋጠመው ችግር ማብራሪያ ሰጥቷል

ነሐሴ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሙምባይ ወደ አዲስ አበባ ለመብረር ሲዘጋጅ በነበረው አውሮፕላን ላይ ስላጋጠመው ችግር ዛሬ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ክስተቱ ትላንት ነሀሴ 10 ቀን 2016 ጠዋት ከህንድ ሙምባይ ወደ አዲስ አበባ ለመብረር በዝግጅት ላይ በነበረ አውሮፕላን ጋሪው ከራምፕ አካባቢ ወደ አውሮፕላኑ በመሄድ ላይ ሳለ እንደተከሰተ ጠቅሷል።

የተፈጠረውን ጉዳይ ሲያብራራ የሚጫኑ ሻንጣዎችን ይዞ ወደ አውሮፕላኑ በመጎተት ላይ በነበረ ጋሪ ላይ ከተጫኑ ሻንጣዎች በአንዱ እሳት ተነስቶ እንደነበር ነው የገለጸው፡፡

ይህንንም ክስተት የተመለከቱ በሙምባይ ያሉ የደህንነት፣ የጸጥታ እና የእሳት አደጋ ባለሞያዎች እሳት የተያያዘውን ሻንጣ በመለየት እሳቱን በቁጥጥር ስር አውለዋል ተብሏል።

አውሮፕላኑ አስፈላጊውን ተጨማሪ የደህንነት ፍተሻ ከተደረገለት እና አስጊ ነገር አለመኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ በረራውን ማካሄዱ ታውቋል።

የሙምባይ ኤርፖርት ባለስልጣናትና የሚመለከታቸው አካላት የክስተቱን ምንጭ በመመርመር ላይ መሆናቸውን የአየር መንገዱ መረጃ አመላክቷል፡፡