በ628 ሚሊዮን ዶላር የሚገነባው የአይሻ-1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ

ነሐሴ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) በ628 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባውና 300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው የአይሻ-1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ፡፡
የኃይል ግዥ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ ከኩባንያው ስራ አስፈፃሚ ሁሴን አልኖዋይስ ጋር የተፈራረሙ ሲሆን የትግበራ ስምምነቱን ደግሞ ከገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ጋር ተፈራርመዋል፡፡
የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ የሚገነባው በሶማሌ ክልል ሲሆን ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ የሚያስችልና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑም ተገልጿል፡፡
አይሻ-I የንፋስ ኃይል ማመንጫ በመንግሥት እና በግል አጋርነት ማዕቀፍ ተግባራዊ የሚደረግ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት መሆኑንም የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ግንባታውን የሚያካሂደው አሚያ የተባለው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ኩባንያ በገባው ውል መሰረት የኤሌክትሪክ ኃይል አምርቶ ለ25 ዓመታት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ የሚያቀርብ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡