ከ95 ሺሕ በላይ ወጣቶች የ“አምስት ሚሊየን ኮደርስ” ስልጠናን በመከታተል ላይ መሆናቸው ተገለጸ

ነሐሴ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ95 ሺሕ በላይ ወጣቶች የ”አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ” የስልጠና መርኃ ግብርን እየተከታተሉ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የ”አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ’’ መርኃ ግብር በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥታት የተጀመረ የዲጂታል ሥራ ክህሎትን የማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ “ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር” በሚል እሳቤ ወጣቶች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ ለማድረግ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ ያስችላል ተብሏል።

ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር)

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የዲጂታል ክህሎት ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡

የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር ይህን መሰረት በማድረግ መዘጋጀቱን ነው ያነሱት፡፡

ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር የተጀመረው ይህ የስልጠና መርሃ ግብር ለስድስት ሳምንታት ስልጠና በመስጠት ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው ተቋም የምስክር ወረቀት የሚገኝበት ነው ብለዋል።

በዚህም ዩዳሲቲ በተሰኘ ተቋም በዳታ ሳይንስ፣ አንድሮይድ ዲቨሎፕመንትና ፕሮግራሚንግ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም ከ95 ሺሕ በላይ ወጣቶች ተመዝግበው ስልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ስልጠናው ለሶስት ዓመታት የሚሰጥ ሲሆን በየአመቱ እያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳደር ምን ያህል ማሰልጠን እንዳለባቸው ኮታ ተሰጥቷቸው እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢንተርኔትና ኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ችግር በሚኖርባቸው ክልሎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መርሃ ግብሩ ትውልድን የመገንባት አካል መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ አኳያ ከመንግስት ባሻገር የግሉ ዘርፍም ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ወጣቶችም ዘመኑ የሚፈልገው ብቁ ዜጋ ለመሆን የሚያስችላቸውን ይህን ስልጠና በመውሰድ ራሳቸውን ተወዳዳሪ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ በስልጠና መርሃ ግብሩ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ 300 ሺሕ ወጣቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።

በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 75 ሺሕ ወጣቶች ሥልጠናውን እንዲከታተሉ ዕቅድ መያዙን ጠቁመው በሐምሌና ነሐሴ ብቻ 60 ሺሕ የሚሆኑ ወጣቶች ሥልጠናውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።