በኢንዱስትሪ ፓርኮች አዳዲስ ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንሰራለን – ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)

 

ነሀሴ 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደሚሰሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጋር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ያለመ ውይይት አድርገዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመትን ለመሳብና ገበያ ለማፈላለግ በፋርማሲዩቲካል፣ በሀይቴክ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በአግሮ ፕሮሰሲግ እና ተያያዥ ኢንቨስትመንቶች ላይ ከፍተኛ ልምድና አቅም ያላቸው አዳዲስ የውጭ ኢንቨስተሮች በፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ኢንቨስት እንዲያደርጉ በመላው ዓለም የሚገኙ ቆንፅላዎች ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆን አንስተዋል፡፡

ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ከምንጊዜውም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በአሰራርና አደረጃጀት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው በሀገራችን ተግባራዊ የተደረጉ ዘርፈ ብዙ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን ለውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይበልጥ ተመራጭ እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ መሰረተ ልማቶች ለኢንቨስትመንት ምቹ አጋጣሚ በመሆናቸው አሟጥጦ መጠቀም ይገባል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል።

አያይዘውም ሚኒስቴሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመስራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ባዛርና አውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ይበልጥ አሟጥጦ ለመጠቀም በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።