የቴሌግራም መስራችና ባለቤት በቁጥጥር ስር ዋለ

ፓቭል ዱሮቭ

ነሐሴ 19/2016 (አዲስ ዋልታ) የቴሌግራም ዋና ስራ አስፈጻሚ እና ባለቤት ፓቭል ዱሮቭ በፈረንሳይ ኤርፖርት በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

የሩሲያ ተወላጁ ፓቭል ዱሮቭ የግል ጀቱ በፈረንሳይ ቦርጌት የአየር ማረፊያ ካረፈ በኋላ ነው በፈረንሳይ ፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡

ዱሮቭ በቁጥጥር ስር የዋለው ከሚያስተዳድረው የመልዕክት መለዋወጫ መተግበርያ ቴሌግራም ጋር በተያያዘ ሲሆን ይህም የቴሌግራም ይዘቶችን በመሀል የሚቆጣጠር አካል (ሞደሬተር) ስለሌለው ነው ተብሏል፡፡

በዚህም ወንጀለኞች መልዕክት ምንም ሳይታወቅባቸው መላላክ በመቻላቸውና ለወንጀለኞች ምቹ እድል በመፍጠሩ ነው በሚል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በፈረንሰይ የሩሲያ ኤምባሲም ጉዳዩን ለማጣራት ፈጣን እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑም ተመላክቷል።

ቴሌግራም በሩሲያ በዩክሬን እና በቀድሞ የሶቪዬት ህብረት አገራት ዘንድ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን በ2018 በሩሲያ መተግበርያው ታግዶ ነበር፡፡ ምክንያቱም ባለቤቱ የተጠቃሚ መረጃ አልሰጥም በማለቱ ነው። ይሁን እንጂ በ2021 እንደገና አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡

1 ቢሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎች ያሉት ቴሌግራም በተለይም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ዋነኛ የኢ-መደበኛ የመረጃ ምንጭ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ስለጦርነቱ የተሳሳቱም ያልተሳሳቱም መረጃዎች እንደሚሰራጩበት እንዲሁም የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪና የሩሲያ መንግስትም እንደሚጠቀሙት ተጠቁሟል፡፡ በዚህም “ምናባዊ የጦር ሜዳ” እስከመባል መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡