የዲጂታል መረጃ ደህንነት ኢትዮጵያን ከማዘመን ባለፈ ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ነሐሴ 25/2016 (አዲስ ዋልታ) የዲጂታል መረጃ ደህንነት ኢትዮጵያን ከማዘመን ባለፈ ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በመገኘት ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት ስርዓትን (PKI) በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት አገልግሎት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከተቋቋመባቸው ቁልፍ ተግባራት ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት አገልግሎት መጀመር የተቋሙን አቅምና እድገት እንደሚያሳይ ጠቁመው በኢትዮጵያ ዲጂታል አሰራርን የተከተሉ በርካታ አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑንና ይህም የዲጂታል ምህዳሩ በፍጥነት እያደገ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የዲጂታል እድገትን የሚመጥን የቨርቹዋል ደህንነት ስርዓት መገንባት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዛሬ በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማትም ይህን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ነው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያዊያን በዘመናት መካከል በውትድርና መስክ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ አኩሪ ታሪክ መስራታቸውን አንስተው፤ ይህም ኢትዮጵያን በቀላሉ የማትደፈር ሀገር እድትሆን አድርጓታል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን አሁን ላይ የሳይበር ጥቃት የሀገራትን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የዲጂታል መረጃ ደህንነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅና ለማጽናት ከሚከናወኑ ቁልፍ ስራዎች መካከል ዋነኛው ስለመሆኑ ነው ያብራሩት፡፡

ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማትም ኢትዮጵያን ከማዘመን ባሻገር ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ ሚናው የጎላ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ እና ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ወደ ተሟላ ምዕራፍ ለማሸጋጋር ታስቦ እየተከናወነ መሆኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአገልግሎት ስርዓቱ በዋናነት ሂሳባዊ ቀመርን በመጠቀም መረጃን መመስጠር እንዲሁም ላኪና ተቀባይ ብቻ በሚያውቁት ሚስጢራዊ ቁልፍ የተመሰጠረን መረጃ መፍታት ላይ ይሰራል፡፡

በተጨማሪም በዲጂታል ሰርቲፊኬት አገልግሎት አማካኝነት ዲጂታል ፊርማ እና የመረጃን ሚስጥራዊነት ማረጋገጥ ያስችላል፡፡