ጀርመን 250 ሺህ ኬንያውያን ሠራተኞችን ልትቀጥር ነው

መስከረም4/2016(አዲስ ዋልታ) የኬንያ እና የጀርመን መንግሥት ባደረጉት የሥራ ስምምነት መሰረት በከፊል እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የሰለጠኑ 250 ሺህ ኬንያውያን ሠራተኞች ወደ ጀርመን ይሻገራሉ ተብሏል።

ኬንያ ለወጣት ባለሙያዎቿ ሥራ እና በቂ ገቢ በማቅረብ ረገድ ችግሮች እየጨመሩባት ነው ሲሆን ጀርመን ደግሞ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ገጥሟታል።

ስምምነቱ የተፈረመው በኬንያዊው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ እና በጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ መካከል ነው።

የበርሊን ባለሥልጣናት ኬንያውያን ሠራተኞች የተፈቀደላቸውን ሥራ ሲጀምሩ ጊዜያዊ የመኖርያ ፈቃድ ያመቻቻሉ ተብሏል።

እንደ ሁለቱ አገራት ስምምነት ከሆነ ኬንያውያን በጀርመን ለትምህርት ወይንም የሙያ ሥልጠና ለማግኘት የረዥም ጊዜ ቪዛ ማግኘት ይችላሉ።

“የረዥም ጊዜ ቪዛቸው በሚያበቃበት ወቅት ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚያስችል እስከ ሁለት ዓመት የሚቆይ ጊዜያዊ የመኖርያ ፈቃድ” እንደሚያገኙ ስምምነቱ ላይ ሰፍሯል።

አክሎም የጊዜያዊ የመኖርያ ፈቃዱ ኬንያውያን ወደ አገር ውስጥ የገቡበትን ዓላማ ካላሳኩ እና “በተወሰነ ጊዜ” የሚሳካ ከሆነ ሊራዘም የሚችልበት እድል አለ ይላል ስምምነቱ።

እንደ ሁለቱ አገራት ስምምነት ከሆነ ኬንያውያን የአይቲ ባለሙያዎች ምንም እንኳን መደበኛ የሆነ የብቃት ማረጋጋጫ ባይኖራቸውም ጀርመን ገብተው መስራት ይችላሉ።

ሁለቱም መንግሥታት የተማሩ ሠራተኞች፣ የሙያ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወይንም ደግሞ የዩኒቨርስቲ ዲግሪያቸው በሌላኛው አካል ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ጀርመን ገብተው እንዲሰሩ ድጋፍ ያደርጋሉ።

ስምምነቱ ሁለቱ አገራት ዜጎቻቸውን መልሶ መቀበል ወይንም የመመለስ ስምምነትም ይዟል።

የሠራተኛ ፍልሰት፣ የጉልበት ብዝበዛ እና የሕገወጥ ሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም የራሱን መመርያ ማተቱን የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።

አምስት የአውቶብስ ሹፌሮች በሰሜን ጀርመኗ ፍሌንስበርግ ፕሮጀክቱን ለመሞከር እንዲሄዱ መደረጋቸውም ተገልጿል።