የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የአዳማ ከተማ የሌማት ቱሩፋት ሥራዎችን ጎበኙ

መስከረም 12/2017 (አዲስ ዋልታ) የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአዳማ ከተማ የሌማት ቱሩፋት ስራዎችን ጎበኙ።
“የህልም ጉልበት ለእምርታዊ እድገት” በሚል መሪ ቃል በአዳማ ከተማ ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የስልጠናው አንድ አካል በሆነው ጉብኝት በአዳማ ከተማ እየተሰሩ የሚገኙ የሌማት ቱሩፋት ስራ እንቅስቃሴን ነው የጎበኙት።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ምርትን ለመጨመርና የስራ እድል ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ክህሎትና ማጎልበት፣ ኢንተርፕሬነርሺፕን ማጠናከርና አርሶ አደሩንና ወጣቶችን ወደ ኢንቨስተርነት ማሸጋገርም ትኩረት የተሰጠው ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዳማ ከተማ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን በማንሳት በተለይም በዶሮ እርባታ፣ የወተት ምርት፣ አሳማ እርባታና የፍራፍሬ ምርት ላይ ጠንካራ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።
በዶሮ እርባታ ስራ በ17 ማዕከላት 544 ሼዶች መሰራታቸውንና 1 ነጥብ 4 ዶሮዎች መግባታቸውን ጠቅሰው ከ9 ሺሕ በላይ ወጣቶችም የስራ እድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የወተት ምርትን ከማሳደግ አንፃርም 357 ላሞች እርባታ ሼዶች መገንባታቸውንና በየቀኑም ከ107 ሺሕ በላይ ሊትር ወተት ለገበያ የሚቀርብ መሆኑን አንስተዋል።
በአጠቃላይ በከተማዋ እየተሰሩ የሚገኙ የሌማት ትሩፋት ስራዎች ከ102 ሺሕ በላይ ሄክታር መሬት ላይ እየተከወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ አመራሮችም እንደ ሀገር አቅሞቻችንን መጠቀም ከቻልን የተሻለ ስራ መስራት እንችላለን በተለይም የጋራ አቅምን፣ የቤተሰብ አቅምንና የመንግስት አቅምን ማዕከል ያደረገ ልማት ማስፋፋት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ታምራት ደለሊ (ከአዳማ)