መስከረም 29/2017 (አዲስ ዋልታ) ኢራን እስራኤል ለምትሰነዝረው ጥቃት የባህረ ሰላጤው አረብ አገራት የአየር ክልላቸውን እንዳይፈቅዱ አስጠነቀቀች፡፡
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በዛሬው ዕለት ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች የፋርስ ባህረ ሰላጤ አገራት በማቅናት ውይይት አድርገዋል፡፡
በዚሁም የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣናት ለእስራኤል ጥቃት የአየር ክልልን ክፍት ማድረግ እርምጃ ሊያስወስድ የሚችል “ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው” ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ኢራን በእስራኤል ያደረሰችውን የሚሳኤል ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል አፀፋ ምላሽ ስጋት እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል።
የየትኛውንም የባህረሰላጤውን አገራት የአየር ክልል ወይንም ወታደራዊ ካምፕ መነሻ ያደረገ ጥቃት በኢራን ላይ ቢደርስ ቴህራን ከጠቅላላው የባህረሰላጤው አገራት የተወሰደ እርምጃ አድርጋ አንደምትወስደው የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ለእስራኤል የሚደረግ ማንኛውም እርዳታ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው እና ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገልጸዋል፡፡
በእስራኤል ላይ ክልላዊ አንድነት እንደሚያስፈልግ እና በቀጣናው መረጋጋትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡