መስከረም 30/2017 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ72 አገሮችና 115 አቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች መካከል በስማርት ሲቲ ንቅናቄ ክፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ከንቲባዎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ኤክስፐርቶችን በመለየት እውቅና የሚሰጠውን የሴኡል ስማርት ሲቲ ሽልማት አሸናፊ ሆኑ፡፡
የስማርት ሲቲ ምርጥ አመራር ሽልማት ተሸላሚ ሊሆኑ የቻሉት የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ህይወት ለማሻሻልና የከተማዋን መሰረተ ልማት ለማዘመን ባሳዩት ቁርጠኝነትና ባስመዘገቡት ውጤት ውጤት መሆኑን በመርኃ ግብሩ አዘጋጆች ተገልጿል፡፡
በተለይም እንደ ኮሪደር ልማት ባሉ ፕሮጀክቶች ለአየር ንብረት ተስማሚ ለሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ቅድሚያ በመስጠት ለሁሉም ነዋሪዎች ምቹ የሆነች አካታች ከተማ ለመገንባት በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማዋን ነዋሪዎችን ኑሮ በማሻሻል ላይ ትኩረት በማድረግ በሰሩት ስራና ባስመዘገቡት ስኬት መሆኑ ተገልጻል፡፡
በተደራራቢ ስራ ምክንያት በመርኃ ግብሩ ላይ መገኘት ያልቻሉት ከንቲባ አዳነች በተወካያቸው የኢኖቬሽ እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ በኩል ባስተላለፉት የምስጋናና የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት “ጊዜያችሁን፣ ጉልበታችሁን ሳትሰስቱ የከተማችንን እና የነዋሪዎቿን ህይወት ለማሻሻል ሌት ተቀን አብራችሁን የሰራች ባለድርሻ አካላት እና ልማት የተባበራችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉ ውጤቱ ሁላችንም መሆኑ ምስጋና ይገባችኋል፤ ሽልማቱ የሁላችንም ነው ማለታቸውን የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።