ጥቅምት 14/2017 (አዲስ ዋልታ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የሀይድሮጂኦሎጂ ጥናት በውሃ እጥረትና በውሃ ጥራት ላይ ለምናደርገው ጥረት ላይ ያለብንን ጫና ለመቀነስ እንደሚያዝ ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ቼክ ሪፐብሊክ የልማት አጋር በጋራ በሲዳማ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌድዮና ጋሞ ዞን ላይ በተዘጋጀው የጂኦሎጂና የሃይድሮጂኦሎጂ ካርታ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በሂደቱ ብዙ ትምህርት የወሰድንበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ የመረጃ አሰባሰብና አያያዝ ስርዓት ላይ ተጨማሪ ግብአት እንደተገኘበት ገልጸዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒሰትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት ያላት ስትሆን የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት የት ቦታ፣ ምን ያህል መጠንና ጥራት እንዳለ ለማወቅ የጂኦሎጂውን ሁኔታ ማጥናት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የጂኦሎጂካል ጥናት የአዲስ አበባ፣ የአርባ ምንጭና ሌሎት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ በማሳተፍ በናሙና ደረጃ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲዮና ጋሞ ዞን አካባቢ ይሰራል ማለታቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
የቼክ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ባለሙያ ለታ አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው የከርሰምድር ውሃ ለኛ ሀገር ወሳኝ በመሆኑ ከሌሎች የውሃ ሀብቶች በቀላሉ ሊለማ የሚችል በመሆኑ ብዙ ጥናትና ቅድመ ዝግጅት የሚፈልግ በመሆኑ ያሉብንን ተግዳሮቶች ለማጥበብ ያግዛል ብለዋል።