126 ኢትዮጵያውያን የባቡር አሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ተሰጣቸው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20/2008 (ዋኢማ)-የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርን የሚያሽከረክሩ 126 ሰልጣኝ ማስተሮች ተመርቀው የብቃት ማረጋገጫቸውን ትናንት ተቀበሉ።

ኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ሳርካ እንደተናገሩት፥ ተመራቂዎቹ በቻይና ለ60 አመታት በዘርፉ ላይ የማሰልጠን አቅም ባለው የቲያንጅን ማሰልጠኛ ኮሌጅ የሰለጠኑ ሲሆን በዚያም ለአንድ አመት የተግባር እና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ወስደዋል።

ሀገር ውስጥ ተመልሰውም የተግባር ስልጠና ለአንድ አመት ያህል አከናውነዋል።

ከመስከረም ወር ጀምሮም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርን የሚያሽከረክሩ 63 ቻይናውያንን ሙሉ ለሙሉ ተክተው የሚሰሩ ይሆናል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ኢንጅነር ጌታቸው በትሩ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በየትኛውም ሀገር የቀላል ባቡርን እንዲያሽከረክሩ የሚያስችል ብቃት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል 18ቱ ሴቶች ናቸው።

መስከረም ወር 2008 በአንድ መስመር ከቃሊቲ እስከ ምኒሊክ አደባባይ ድረስ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ያለው የባቡር መስመርም ለተሳፋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል።

የቀላል ባቡሩ በአሁኑ ወቅት በየቀኑ ከ300 እስከ 400 ሺህ ብር ገቢ እያገኘ ነው።(ኤፍ.ቢ.ሲ)