የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 18 ሺህ 496 የ40/60 ፕሮግራም ቤቶችን እንደሚያስተላልፍ ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ሠራተኞች በመስሪያ ቤቱ የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይተዋል።
ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ቀደም ሲል ግንባታቸው የተጀመሩ 37 ሺህ 498 የ40/60 እና 132 ሺህ 702 የ20/80 ፕሮግራም ቤቶችን አፈጻጸም 45 በመቶ ለማድረስም አቅዷል።
በግንባታ አፈጻጸም ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ርዕሰ–ጉዳዮች ዙሪያም ስድስት ጥናቶችን ያከናውናል።
የከተማ ቤቶች መረጃ አስተዳደርን ለማጎልበትም በበጀት ዓመቱ የ200 ሺህ የመንግስትና የጋራ ህንፃ ቤቶች መረጃ ይሰበሰባል።
ሚኒስትር መኩሪያ ኃይሌ በውይይቱ ወቅት "የህብረተሰቡን ችግር ከመፍታት አኳያ በጊዜ የለንም መንፈስ ልንሰራቸው የሚገቡ ብዙ ስራዎች አሉ" ነው ያሉት።
ሚኒስቴሩ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በቤት አቅርቦት ፣ ለባለሃብቶችና ለሌሎች መሰረተ ልማቶች መሬት በማቅረብ ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሮችና የክልል መንግስታት እነዚህን ጉዳዮች በፍጥነት እንዲሄዱባቸው ሚኒስቴሩ የበኩሉን ድርሻ ይጫወታል ብለዋል።
በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 1 ሺህ 126 ሄክታር የለማ መሬት፣ 1 ሺህ 782 ሼድ፣ 72 ህንጻና ሶስት የገበያ ማዕከላት ግንባታ መከናወኑን በክትትልና ድጋፍ በማረጋገጥ ግብረ መልስ ይሰጣል ተብሏል።(ኢዜአ)